የ NWHMC ፖሊሲ -


የ NWHMC ፖሊሲ - (PDF)​

 1. ፖሊሲ
 2. የ Northwest Hospital & Medical Center (NWHMC) ተልዕኮ፣ ለሰሜን Seattle ማህበረሰብ ጥራት ያለው የጤና እንክብካቤ አገልግሎት በማቅረቢያ ጥበብና አገልግሎት ላይ መሳተፍ ነው። ይህንን ተልዕኮ ለመፈጸም፣ ሐኪም ቤቱ የሚከተሉትን የሚያደርግ የዕዳ ክፍያ ስብሰባ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲሆን ይጠይቃል፥

  1. ለተሰጡት አገልግሎቶች በተመደበው ሰዓት ውስጥ ክፍያ እንዲከፈለው የሚያበረታታ።
  2. እያንዳንዱ ግለሰብ ያለውን የፋይናንስ ሁኔታ በግምት ውስጥ የሚያስገባ።
  3. ታካሚዎች የክፍያ ግዴታቸውን እንዴውጡ የተለያዩና በቂ አማራጮችን የሚሰጥ።

  የታካሚ ፋይናንስ አገልግሎቶች (Patient Financial Services (PFS)) ባልደረቦች ከታካሚዎች ጋራ በሚሰሩበት ወቅት ይህ ፖሊሲ ምሪት ይሰጣቸዋል። በዚህ ፖሊሲ ውስጥ ላልተገለጹት ሁኔታዎች የታካሚ ፋይናንስ አገልግሎቶች ዲሬክተር (Director of Patient Financial Services) ወይም የታካሚ ፋይናንስ አፈጻጸም ዲሬክተር (Director of Financial Operations) ውሳኔዎችን ያመቻቻል ወይም ያጠናቅቃል።

  ለዚህ ፖሊሲ ጉዳይ ‘ታካሚ’ የሚለው ቃል የሚታከመውን ግለሰብ ወይም ሒሳቡን ለመክፈል ሕጋዊ ኃላፊነት ያለበትን ሌላ ማንኛውንም ወገን ያመለክታል።

 3. የፖሊሲ መግለጫ አጭር ዝርዝር
 4. የ NWHMC ፖሊሲ ለተሰጡት አገልግሎቶች ሙሉ ክፍያ እንደሚከፈል መገመት ነው። በመድን ዋስትና ላልተሸፈኑ ቀሪ የሂሳብ መጠኖች ታካሚው ከሐኪም ቤት መጀመሪያ ከወጡ በኋላ የቢሉን ሙሉ ክፍያ መከፈል አለባቸው፣ ከታካሚ ፋይናንስ አገልግሎቶች ጽ/ቤት (Patient Financial Services Department) ጋራ የክፍያ ስምምነት ላይ ተደርሶ ካልሆነ በቀር።

  1. ገቢ የሚደረግ የአካውንት ሂሳብ መጠንን ዜሮ ማድረጊያ አማራጮች
  2. ገቢ የሚደረግ የአካውንት ሂሳብን ዜሮ ማድረጊያ 8 አማራጮች አሉ፥

      አማራጮቹ    የፖሊሲ ምሪት
      ክፍያ ሂሳቡ ከተሰረዘ    የክፍያ ፖሊሲ
      ኮንትራቱ ከተሻሻለ    የመድን ዋስትና ኮንትራት 
      ግብረ ሰናይ    የፋይናንስ እርዳታ ፖሊሲ
      አስተዳደራዊ/ሌላ ማሻሻያ    የማሻሻያ ፖሊሲ
      የመድን ዋስትና ክፍያ    የክፍያ መሰብሰቢያ ፖሊሲ
      ታካሚ ክፍያ ሲያደርግ    የክፍያ መሰብሰቢያ ፖሊሲ
      መጥፎ ዕዳ - የኤጀንሲ-ያልሆነ/ሌላ    የክፍያ መሰብሰቢያ ፖሊሲ
      መጥፎ ዕዳ - የክፍያ ሰብሳቢ ኤጀንሲ    የክፍያ መሰብሰቢያ ፖሊሲ

  3. ለታካሚዎች የሚደረግ የፋይናንስ ማጣሪያ፥
  4. ታካሚዎች የፋይናንስ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ብቁ ለመሆናችው ውሳኔ ለማድረግ፣ ወደ ሐኪም ቤት ከመግባታቸው በፊት ወይም በሚገቡበት/በምዝገባ ወቅት ላይ ማጣሪያ ይደረጋል፣ ቢሆንም ድንገተኛ የጤና ሁኔታ ላጋጠማቸው ታካሚዎች የፋይናንስ ሁኔታቸው ከመጣራቱ በፊት ሕክምና ተደርጎላቸው የጤና ሁኔታቸው እንዲረጋጋ ይሆናል። የሥራ ባልደረቦች ስለ ታካሚው የክፍያ ድርሻ የሚያረጋግጡበትን ሃቀኛና የተሟላ አሃዛዊ መረጃ ታካሚዎች ማቅርብ ይጠበቅባቸዋል። ስለ ታካሚው ኃላፊነት አንዴ ውሳኔ ከተደረገ በኋላ፣ የሥራ ባልደረቦች ለታካሚው ወዲያዉኑ የማሳወቅ ግዴታ አለባቸው።

   የፋይናንስ ማጣሪያ ከሚከተሉት ውስጥ የተወሰኑትን ወይም ሁሉንም ተግባሮች ያጠቃልላል፥

   1. የፋይናንስ የስነ ሕዝብ (ዲሞግራፊ) መረጃን መሰብሰብ።
   2. ስለ መድን ዋስትና ብቁነትና ጥቅሞች ውሳኔ ማድረግ።
   3. በሚስጥር ተቀማጭ የፋይናንስ መረጃ ቅጽን (Confidential Financial Information Form) መሙላት።
   4. የመድን ዋስትና መፍቀጃ ቁጥሮችንና መምሪያን ማግኘት።
   5. ታካሚው ያለበትን ቀሪ ዕዳ ዜሮ የሚያደርግበትን ዕቅድ ማውጣት።
   6. በታካሚው የመድን ዋስትና ዕቅድ በተፈቀደው መሰረት፣ ለተቀናሽ ክፍያ (ዲደክተብል) እና መቀናጆ ኢንሹራንስ (ኮ-ኢንሹራንስን) ተያዥ ገንዘብ መቀበል።
   7. ታካሚው በ NWHMC ስለነበረው ያለፈ የክፍያ ታሪክ መገምገም።
  5. ተያዥ ገንዘብን መሰብሰብ፥
  6. በተደረገው የፋይናንስ ማጣሪያና ግለሰቡ እንደሚከፍል በተገመተው ቀሪ መጠን መሰረት፣ ልክ መጠኑ እንደ ተወሰነ ወይም በታካሚው የመድን ዋስትና እቅድ በሚፈቅደው መሰረት ተያዥ ገንዘብና የተገመተውን የኢንሹራንስ መቀናጆ ቀሪ ክፍያ መጠየቅ የ NWHMC ፖሊሲ ነው። ታካሚዎች ለሚያገኙት እንክብካቤ አስቀድመው መክፈል እንዲችሉ አካውንት ሊከፈትላቸው ይችላል። በእንክብካቤ ወቅት ወይም ከሕክምና ስንበት ወቅት ክፍያዎች ሊሰበሰቡ ይችላሉ። በድንገተኛ የሕክምና ክፍል ውስጥ፣ ተያዥ ገንዘብ የሚጠየቀው፣ የሕክምና አገልግሎት ከተሰጠና የታካሚው ሁኔታ ከተረጋጋ በኋላ ብቻ ነው። ሁሉም ክፍያዎች እንዲከፈሉ በሚጠየቅበት ወቅት የታካሚውን ሁኔታ በግምት ውስጥ በማስገባትና፣ የሐኪም ቤቱን ፖሊሲዎች ሁሉ ተከትለን ነው።

   የመቆነጃጃ (ኮስሜቲክ) ወይም የግድ-አፈስላጊ ያልሆኑ የሕክምና አገልግሎቶች አገልግሎቱ ከመሰጠቱ በፊት ሙሉ በሙሉ መከፈል ይኖርበታል። ለልዩ ሁኔታዎች ስለ ሙሉ ክፍያ አስተያየት ሊደረግ ይችል ይሆናል፣ ቢሆንም ግን በታካሚ ፋይናንስ አገልግሎቶች ወይም በታካሚ መቀበያ ክፍል ዲሬክተር (Director of Patient Financial Services/Patient Access) ፈቃድ መሰጠት ይኖርበታል።

  7. አጠቃላይ የመሰብሰቢያ ደንብ፥
  8. ያልተከፈለ ቀሪ የሂሳብ መጠንን ሁሉ ከሕክምና ከወጡ በኋላ የሚላክልዎትን ቢል ልክ እንዳገኙ መከፈል ይኖርብዎታል፣ ከሚከተሉት በገዛ-ራስ የመክፈያ ልዩ አስተያየቶች በስተቀር፥

   1. ይህንን ፖሊሲ ተከትሎ፣ የሚደረጉ የክፍያ እቅድ መሰናዶዎች።
   2. ተጨማሪ የፋይናንስ ማጣሪያ እየተደረገ ከሆነ።
   3. የሐኪም ቤት የቢል አደራረግ ስህተት፣ መዘግየት፣ ወይም መፍትሔ ያላገኙ የቢል ክፍያ ክርክሮች ካሉ።
   4. ያልተከፈለ የመድን ዋስትና ጥያቄዎች በመኖራቸው ሳቢያ፣ የታካሚው ቀሪ ዕዳ መጠን በቀላሉ ሊታወቅ ካልተቻለ።
  9. የመድን ዋስትና ቢል አደራረግ ፖሊሲ፥
  10. የ NWHMC፣ የታካሚ ፋይናንስ አገልግልቶች (Patient Financial Services) የስቴት፣ የፌደራልና የመድን ዋስትና እቅዶች ባለ ኮንትራት ቢሉን እንዲከፍሉ ያደርጋል። ታካሚው ተፈላጊውን መረጃ በሚያመጣ ጊዜ ሌሎች የክፍያ ምንጮችም ቢሉን እንዲከፍሉ ይደረጋሉ።

  11. ያልተከፈሉ የታካሚ ቀሪ ዕዳዎች፥
  12. በታካሚ ሒሳብ ላይ ያሉ ቀሪ ዕዳዎች፣ ከታካሚ ፋይናንስ አገልግልቶች (Patient Financial Services) ጋራ ሌላ ስምምነት ላይ ተደርሶ እስካልነበረ ድረስ፣ ታካሚው ከሕክምና ከወጣ በኋላ ልክ ቢል እንደ ደረሰው መከፈል ይኖርበታል። ከመድን ዋስትና አቅራቢዎች ጋራ፣ ክፍያው እንዳይከፈል ውድቅ ለሆነበት ይግባኝም ጨምሮ፣ ለሚኖሩት ጉዳዮች ሁሉ መፍትሔ እስከምናገኝ ድረስ ታካሚው ቢሉን እንዲከፍል በኃላፊነት ተጠያቂ አናደርገውም። ክፍያው በታካሚው መከፈል አለበት ብለን ጥያቄያችንን ከመቀየራችን በፊት፣ ከመድን ዋስትና ሰጪው ክፍያውን ለመሰብሰብ እንደ የታካሚው ጠበቃ ሆነን እንከራከራለን፤ ቢሆንም ግን፣ ለሚኖሩ የመድን ዋስትና ጥያቄዎች ኃላፊነት መሸከም ወይም በክርክር ላይ ላሉ ጥያቄዎች ተከራክረን ስምምነት ላይ ለማድረስ ኃላፊነትን አንወስድም።

   የሂሳብ ስብሰባ እርምጃ ከማስወሰዳችን በፊት፣ የእንክብካቤ ጥራትና የቢል አደራረግ ትክክለኝነት ጉዳዮች በተቻለ መጠን በቶሎ መፍትሔ ማግኘት ይኖርባቸዋል።

   የፋይናንስ ችግር እንዳለባቸው የሚያሳውቁ ሁሉም ታካሚዎች፣ የፋይናንስ እርዳታና/ወይም ምናልባትም የ Medicaid ሽፋን ማጣሪያ ይደረግላቸዋል። የፋይናንስ እርዳታ በማንኛውም ግዜ ላይ ሊሰጥ ይችል ይሆናል፣ ጉዳዩ ወደ ዕዳ ሰብሳቢ ኤጀንሲዎች ከተላለፈ በኋላም እንኳ።

 5. ታካሚ ቀሪ የዕዳ መጠንን ለመክፈል ያሉት አማራጮች
  1. የክፍያ መንገዶች፥
   NWHMC፣ ጥሬ ገንዘብ፣ ቼክ፣ ወይም Visa/MasterCard ለክፍያ ይቀበላል። የክሬዲት ካርድ ክፍያዎችን በስልክ ወይም በኢንተርኔት በኩል ባሉ የቢል መክፈያ አማራጮች እንቀበላለን። የታካሚው የክፍያ ድርሻ ከሕክምና ከወጣ በኋላ የመጀመሪያው ቢል እንደ ደረሰው መከፈል ይኖርበታል፣ የመክፈያ መንገድ ስምምነቶች ካሉ ወይም ለፋይናንስ እርዳታ ማመልከቻ ገብቶ ከነበረ በስተቀር።
  2. የክፍያ እቅዶች፥
   የክፍያ መንገድ ስምምነቶች  የሚመሰረቱት ታካሚው ለታካሚ የፋይናንስ አገልግልቶች ጽ/ቤት (Patient Financial Services Department) ጥያቄ ሲያቀርብ ነው። ለወትሮው፣ ይህ እስከ 12 ወራት ድረስ እኩል ክፍያ የሚከፈልበትን ጊዜ የሚፈቅድ ይሆናል፣ ፈቃድ የተሰጣቸው ሁኔታዎች ተፈጻሚ ከሆኑ ደግሞ ከዚያ በላይ ሊወስድ ይችላል።
   1. ለክፍያ መንገድ ስምምነቶች ፈቃድ የሚያስፈልገው በሚስጥር ተቀማጭ የፋይናንስ ቅጽን (Confidential Financial Form (CFF)) ከ 12 ወራት በላይ ለማራዘም።
  3. ወደ ገንዘብ ሰብሳቢ ኤጄንሲ ጉዳይ መምሪያዎች፥
   bጉዳዩ ወደ ሰብሳቢ ኤጀንሲዎች እንዲመራ አስፈላጊ የሚሆነው፣ ታካሚው የተስማማበትን የፋይናንስ ውል ለማክበር ፈቃደኛ ካልሆነ፣ የፋይናንስ ውሉን ከሰበረ፣ ከመድን ዋስትና ያገኘውን ገንዘብ ለሐኪም ቤቱ ካላስተላለፈ፣ ወይም በ NWHMC (የገንዘብ ሂሳብ ስብሰባ መምሪያ ነጥቦች) ያለው የክፍያ-እምቢተኝነት ታሪክ ካለው ነው። የታካሚ ሒሳቦች ወደ ሰብሳቢ ኤጀንሲ የሚዛወሩት የ Customer Service Supervisor ግምገማ ካደረገና ታካሚው ከሐኪም ቤት ከወጡ በኋላ የመጀመሪያ ቢሉ ለታካሚው/ለዋሱ በፖስታ ከተላከ ከ 120 ቀኖች በኋላ ይሆናል።
  4. ታካሚው ከሐኪም ከወጣ በኋላ የመጀመሪያ ቢል ከመድረሱ ከ 120 ቀን በፊት፣ ጽሕፈት ቤቱ ሒሳቡን ወደ ሰብሳቢ ኤጀንሲዎች እንዲመራ የሚፈቅዱ የተወሰኑ ልዩ ሁኔታዎች አሉ፥

   1. ለፋይናንስ እርዳታ ብቁነት ውሳኔ ከተሰጠና ለግለሰቡ ስለተቀነሰው ቀሪ ዕዳ መጠን ወይም ለፋይናንስ እርዳታ ብቁ አለመሆኑ ተነግሮት ግን የፋይናንስ ክፍያ ስምምነቶችን ለማክበር ፈቃደኛ ካልሆነ (ወይም ከላይ ከተጠቀሱት የገንዘብ ሂሳብ ስብሰባ መምሪያ ነጥቦች ውስጥ ቢያንስ አንዱን የሚያሟላ ከሆነ)።

   2. ታካሚው ላገኘው እንክብካቤ መክፈል ካለበት ሙሉ መጠን ያነሰ እንዲከፍል ብቁ እንደሚሆንና፣ ለተጨማሪ የፋይናንስ እርዳታ ማመልከቻ የማስገባት መብት እንዳለው ከተነገረው፣ ግን በተፈቀደው ተገቢ የግዜ ገደብ ወቅት ማመልከቻውን ሳያስገባ ሲቀር።

   3. ምንም የክፍያ እቅድ ስምምነት ካልተደረገ – ከቀረቡት የክፍያ እቅዶች ውስጥ አንዱን መቀበል ያልቻሉ ታካሚዎች/ዋሶች፣ ከተገቢው ማስታወቅያ ጋር ጉዳያቸው ወደ ሰብሳቢ ኤጀንሲ ይመራል።

   4. ለሚላኩት ደብዳቤዎች ወይም የስልክ ጥሪዎች መልስ ካልተገኘ – አንድ ታካሚ በፖስታ የሚላኩ ቢሎችና ጽሁፎች እንደሚደርሱት ከታወቀና ለሐኪም ቤቱ መልስ የማይሰጥ ከሆነ፣ ሐኪም ቤቱ ሒሳቡን እንደሚያዛውር የሚገልጽ ተገቢ ማስታወቅያ ታካሚው እስከደረሰው ድረስ፣ ሒሳቡ አገልግሎት ከተሰጠ ከ 90 ቀኖች በኋላ ሊዛወር ይችላል።

   5. የተገባው ውል ካልተከበረ – ከተመደበ ክፍያ በታች ክፍያ የሚያደርጉ ወይም ክፍያን ሳይከፍሉ የሚያሳልፉ ታካሚዎች፣ ተገቢው ማስታወቅያ ከተላከላቸው በኋላ ወደ ኤጀንሲው ይመራሉ።

   6. ታካሚው እንደ ተሰወረ ከተወሰነ – ትክክለኛ ወይም የተሟላ የመገናኛ መረጃ የማይተዉ ታካሚዎች፤ ይህ ውሳኔ ልክ እንደ ተላለፈ ወዲያዉኑ ጉዳያቸው ወደ ኤጀንሲው ሊተላለፍ ይችላል። በምዝገባ ወቅት ስህተት ተፈጽሞ እንዳይሆን ለማረጋገጥ፣ የተሰወረውን ፈልጎ ለማግኘት ሙከራ መደረግ ይኖርበታል።

   7. ታካሚው አጥጋቢ ያልሆነ የክፍያ ታሪክ ካለው – ለሐኪም ቤቱ ዕዳን ያለ-መክፈል ታሪክ ያላቸው ታካሚዎች (ለምሳሌ፣ ሌላ የኤጀንሲ ሒሳቦች ካለው)፣ ተገቢው ማስታወቅያ እስከደረሳችው ድረስ፣ ጉዳያቸው ከ 90 ቀኖች ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሊተላለፍ ይችላል።

   8. ከዚህ በፊት ታካሚው ያልከፈላቸው ዕዳዎች ካሉ – ተከታታይ ውሎችን ያፈረሱ ታካሚዎች፣ ከዚህ በፊት ሳይከፍል የቀረው ዕዳ ጉዳያቸውን ወዲያዉኑ እንደሚያስተላልፍ እስከተነገራቸው ድረስ፣ ጉዳያቸው ወደ ኤጀንሲ ከመዛወሩ በፊት ተጨማሪ ማስታወቅያ እንዲላክላቸው አስፈላጊ አይሆንም።

   የ PFS ባልደረባ፣ ይህ እርምጃ እንዲቆም የሚጠይቁ ልዩ ሁኔታዎች እንዳሉ ከወሰነ፣ ይህ ወደ ሰብሳቢ ኤጀንሲ የሚደረግ አፋጣኝ ምደባ እንዲቆም ሊደረግ ይችል ይሆናል።

  5. ልዩ የሆኑ የዕዳ ስብሰባ እርምጃዎች (Extraordinary Collection Actions) (ECAs)፥
  6. የሚከተሉት እስከሚፈጸሙ ድረስ፣ የታካሚ ሒሳቦች ላይ ማንኛውም የ ECA እርምጃዎች ተፈጻሚ አይሆኑም1፣ የ NWHMC ወይም የተመደቡበት ሰብሳቢ ኤጀንሲ እርምጃ ተፈጻሚ አይሆንምባቸውም፥

   1. የፋይናንስ እርዳታ ብቁነትን ለመወሰን ተገቢ የሆኑ ጥረቶች እስከሚደረጉ ድረስ። ተገቢ የሆኑ ጥረቶች ሲባሉ የሚከተሉትን ያጠቃልላሉ22
    1. ለታካሚው ግልጽ ሊሆን በሚችል ቋንቋ የተጻፈ የፋይናንስ እርዳታ ፖሊሲ አጭር ዝርዝርና ከሐኪም ቤት ከመውጣቱ በፊት የፋይናንስ እርዳታ ማመልከቻ ከቀረበለትና ማመልከቻውን ለመሙላት እርዳታ ከተደረገለት፤

    2. ያልተሟላ ማመልከቻ ከደረሰን፣ ስላልተሟላው መረጃ/ሰነድ የሚገልጽ የጽሑፍ ማስታወቅያ፣ ማናቸውንም ECA ዎች ጨምሮ፣ ለታካሚው ከተላከ

     ማመልከቻ ወይም ክፍያ በተወሰነ የግዜ ገደብ ውስጥ ካልደረሰው፣ ሐኪም ቤቱ (ወይም የሐኪም ቤቱ ወኪል) ሂደቱን ሊያነሳሳ ወይም ሊጀምር ይችላል፤3
    3. ሁሉም የቢል መግለጫ ጽሁፎች፣ የፋይናንስ እርዳታን የሚመለከትና ለመረጃ/እርዳታ ለማግኘት የስልክ ቁጥር ያለበትንና የፋይናንስ እርዳታ ሰነድ ኮፒዎች የሚገኙበት የቀጥታ ድረገጽ አድራሻ የተጻፈበት ግልጽ የሆነ ማስታወቂያን ይዘዋል፤

    4. ለፋይናንስ እርዳታ የሚገቡ ማመልከቻዎች በተገቢው የግዜ ገደብ ውስጥ ተፈጻሚ የሚሆኑ ሲሆን፣ ለታካሚውም ስለውሳኔው በጽሁፍ ማስታወቂያ ይሰጣል፣ የቀሪ ዕዳና ተመላሽ የሆነ የማንኛውም እላፊ ክፍያ ወቅታዊ የቢል መግለጫ ካለ።

    5. ሐኪም ቤቶች፣ ታካሚው ለአንድ ወይም ከዚያ በላይ ለሚሆኑ በገቢ አቅም ለተመደቡ የመንግስት እርዳታ ፕሮግራሞች ብቁነት በመሠረተው መረጃ መሰረት፣ ሊገኝ ስለሚችል በጣም ለጋስ የፋይናንስ እርዳታ ታካሚው ብቁ ለመሆኑ ውሳኔ በማድረግ የተገቢ ጥረቶች መስፈርትን ሊያሟሉ ይችላሉ።

    6. ሐኪም ቤት፣ በፋይናንስ እርዳታ ማመልከቻ ላይ የተጠየቀውን መረጃ/ሰነድ ሙሉ በሙሉ ለማቅረብ ላልቻለ አንድ ታካሚ የፋይናንስ እርዳታ ለመስጠት ምርጫ ማድረግ ይችላል።
   2. ከሐኪም ቤት ከወጣ በኋላ የመጀመሪያው የቢል መግለጫ ከተላከበት ቀን ጀምሮ 120 ቀኖች ካለፉ፤ እና

   3. የሚከተሉት የማሳወቂያ ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉ (የ ECA ከመጀመሩ ቢያንስ ከ 30 ቀኖች በፊት)፥
    1. የፋይናንስ እርዳታ መኖሩን የሚገልጽ በጽሑፍ የተዘጋጀ ማስታወቅያ ተልኳል፤
    2. ግልጽ በሆነ ቋንቋ የተዘጋጀ የፋይናንስ እርዳታ ፖሊሲ አጭር ዝርዝር ከተሰጠ፤
    3. ክፍያ አለመከፈሉ ከተገለጸ በኋላ ለሚደረግ እርምጃ(ዎች) ማስታወቅያ ከተሰጠ፤
    4. ክፍያ ካልደረሰ፣ ከየትኛው ቀን ጀምሮ እርምጃ(ዎች) እንደሚወሰድ(ዱ) የሚያሳስብ ማስታወቅያ፣ እና
    5. ስለ ፋይናንስ እርዳታ ፖሊሲና የፋይናንስ እርዳታ ማመልከቻ ከታካሚው ጋራ የቃል ውይይት ለማድረግ ሙከራዎች ከተደረገ።
   4. ከሐኪም ቤት ከወጣ የመጀመሪያው ቢል ከተላከበት ከ 150 ቀኖች በኋላ ስለ ክሬዲት ሪፖርት ማድረግ ይጀመራል።

   5. ሳይከፈል ግዜ ላለፈበት ቢል፣ ከሐኪም ቤት ከወጣ የመጀመሪያው ቢል መግለጫ ከተላከበት ከ 240 ቀኖች በፊት ክስ ላይመሰረት ይችላል።

   6. የታካሚ ፋይናንስ አገልግሎቶች ወይም የታካሚ መቀበያ ዲሬክተር (Director of Patient Financial Services/Patient Access)፣ ታካሚው ለፋይናንስ እርዳታ ያለውን ብቁነት ለመወሰን ተገቢው ጥረት መደረጉን ይወስናል።
 6. ወዲያዉ ከገዛ-ራስ ለሚከፈል ክፍያ የቅናሽ ሂሳብ ፖሊሲ፥
 7. የታካሚ ቢል አስከፋይ ክፍል ለክፍያ መንገዶች ድርድር ለማድረግና የታካሚዎቻችን ፍላጎቶችንና ግምትን ለማሟላት የሚያስችሉት የተለያዩ መንገዶችን ለማሰናዳት እንዲያስችል ሆኖ የሐኪም ቤቱ የዕዳ ሰብሳቢ ፖሊሲ በግልጽ ተቀምጧል። ከዚህ በታች የተገለጸው የቅናሽ ዋጋ በመጀመሪያ ደረጃ የሚፈቀደው፣ የመድን ዋስትና ሽፋን ሳይኖራቸው ላገኟቸው አገልግሎቶች ወዲያዉ ክፍያ ለከፈሉ ታካሚዎች ምላሽ ለመስጠት ነው።

  አንድ ታካሚ/ዋስ፣ ለቀረቡ አገልግሎቶች ምንም የመድን ዋስትና ሽፋን ሳይኖረው፣ ለሚደርሰው ቢል በሰላሳ (30) ቀኖች ውስጥ
  ቢሎቹን ከከፈለ ሰላሳ (30) በመቶ ቅናሽ ይደረግለታል። ቢሆንም ወዲያው ክፍያን የማይመለከተው፣ የ NWHMC Packaged Pricing Programs (ለምሳሌ፣ የመቆነጃጃ (ኮስሜቲክ) አገልግሎቶች፣ እና የስፒሻልቲ ቀዶ ጥገና)፣ ወይም ለታካሚዎች/ለዋሶች

  የተሰጠ ችሮታን/የፋይናንስመረጃው አስተማማኝ ወይም ስህተት ወይም የተገኘው ታካሚውን በማስጨነቅ ወይም በማስፈራታት መሆኑን ያሳምናል በሚለው መረጃ መሠረት ከሆነ ነው። 

  በሐኪም ቤት ውስጥ የድንገተኛ ሕክምና ክፍልንና የታካሚ መቀበያ ክፍልን ጨምሮ የታካሚ መገልገያ ቦታዎች፣ በግላቸው ለሚከፍሉ ታካሚዎች ሁሉ የክፍያ አማራጮች መረጃ ይሰጣሉ። እነዚህ የክፍያ አማራጮች፣ ወዲያዉኑ ሲከፈል ስለሚደረጉ ቅናሾች፣ ስለ ፋይናንስ እርዳታዎች፣ እንዲሁም ለሜዲኬድ ማመልከቻ ለማስገባት እርዳታ የመግኛ መረጃን።

 8. ሁሉንም ታካሚዎች/ዋሶች እኩል ማስተናገድ፥
 9. የ Northwest Hospital and Medical Center፣ የታካሚዎችን አካውንት (ሒሳብ) የሚያስፈጽመው በዚህ የዕዳ ስብሰባ ፖሊሲ መሠረት ነው። በምንም ዓይነት ሁኔታ፣ ይህ ፖሊሲ በተግባር ላይ በሚውልበት ወቅት ዕድሜ፣ ዘር፣ የቆዳ ቀለም፣ ሀይማኖት፣ ጾታ፣ ጾታዊ ዝንባሌ ወይም የትውልድ ሀገር በግምት ውስጥ አይገባም።

  የዚህን ፖሊሲ ግልባጭ፣ እንዲሁም የፋይናንስ እርዳታ ፖሊሲ፣ የፋይናንስ እርዳታ ፖሊሲ አጭር ዝርዝር እና የፋይናንስ እርዳታ ማመልከቻ ግልባጮችን የሚከተሉትን የታካሚ ፋይናንስ አገልግልቶችን (Patient Financial Services) በማነጋገር ማግኘት ይቻላል፥

  UW Medicine/NW Patient Financial Services 10330 Meridian Ave. N, Suite 260
  Seattle, WA 98133
  206/668-6440 ወይም በነጻ ስልክ መሥመር 877/364-6440
  nwhospital.org/visitorinfo/billing/asp

  የተገመገመው፥ 10/05፣ 9/06፣ 8/07፣ 11/07
  የተከለሰው፥ 6/92፣ 7/93፣ 3/96፣ 6/01፣ 9/06፣ 8/07፣ 11/07፣ 2/11፣ 3/13፣ 3/15፣ 4/16፣ 10/17
  የአፈጻጸም ኃላፊነት/ፈቃድ፥
  የታካሚ ፋይናንስ አገልግልቶች ዲሬክተር፣ እና የገቢ ገንዘብ ደረጃ ዋና ዲሬክተር እና የሥራ አስኪያጅ መሪነት ጓድ ዋና የፋይናንስ ሹም፥ የሥራ አፈጻጸም ዋና ምክትል ፕሬዚደንት
  የሥራ አስኪያጅ መሪነት ጓድ፥ የክልኒክ አገልግልቶች ምክትል ፕሬዚደንት/ሲ ኤን ኦ


1 ECA ዎች የሚያጠቃልሉት፣ ግለሰቡን ወደ ክሬዲት ኤጀንሲዎች ሪፖርት ማድረግ፣ ቤት ንብረቱን በዕዳ መያዝ፣ የባንክ ሒሳቦችን ማያያዝ፣ የፍታብሔር ሕግ እርምጃዎችን መጀመር፣ ከደሞዝ ተቆራጭ መውሰድ እና አስፈላጊ የሚሆን የሕክምና እንክብካቤ ከመሰጠቱ በፊት ክፍያ ወይም መያዣ ገንዘብ መጠየቅን ያጠቃልላሉ።

2 ሐኪም ቤት፣ ከታካሚ የፈቃድ መስጫ ፊርማ በማግኘቱ ብቻ፣ የታካሚውን ብቁነት ለመወሰን ተገቢ የሆነ ጥረት ለማድረግ ሳይችል፣ ወይም ሐኪም ቤቱ ተገቢውን ጥረት እንዳላደረገ የሚቆጠረው ሐኪም ቤቱ ለእርዳታ ብቁ አለመሆን ውሳኔን የሰጠው

3 በ ECAዎች የተጀመሩ ማናቸውም ነገሮች እንዲቆሙ ይደረጋሉ።